Home Uncategorized “አሳፋሪ የአማተሮች ትያትር ነው የተሰራብኝ ”- አቶ ልደቱ አያሌው

“አሳፋሪ የአማተሮች ትያትር ነው የተሰራብኝ ”- አቶ ልደቱ አያሌው

0
“አሳፋሪ የአማተሮች ትያትር ነው የተሰራብኝ ”- አቶ ልደቱ አያሌው

ላለፉት ሶስት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው፤ ፖሊስ ሊፈታቸው ባለመፍቀዱ በፍርድ ቤት በዋስትና ጉዳይ ላይ ያለው ክርክር ቀርቶ ሌላው የፍርድ ሂደት እንዲቀጠል ጠየቁ። ሕገ መንግስቱን በጣሱ መልኩ የፍርድ ቤት ውሳኔን ሳያስፈጽሙ የቀሩ አካላትን በተመለከተ “አሁን እየተሰራ ያለው የአማተሮች ትያትር ነው” ሲሉ እርምጃቸውን አጣጥለዋል። 

https://zolandoshop.com/necklace/

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል የቀረበባቸውን ክስ በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ልደቱ፤ በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥላቸውም ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙ የማይፈጸም ከሆነ በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከትላንት በስቲያ ሰኞ በዋለው ችሎት አስጠንቅቆ ነበር።  

ያስያዙት የ100 ሺህ ብር ዋስትና ተከብሮላቸው ከእስር ሳይለቀቁ የቀሩት አቶ ልደቱ፤ በዛሬው የችሎት ውሎ ጠንከር ባለ ጽምጸት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል። የዞኑ ፍርድ ቤት የህግ የበላይነትን  ለማስከበር አቅሙ የፈቀደውን ያህል ላደረገው ጥረት አክብሮታቸውን የገለጹት ዕውቁ ፖለቲከኛ፤ የፍርድ ቤቱን “ውድ ጊዜ”፣ እርሳቸው “ትያትር” ሲሉ በጠሩት ድርጊት ማባከን እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።

“ከዚህ በኋላ ለታሪክ፤ ፖሊስ ሕገ መንግስቱን ጥሶ፣ የእኔንም መብት ጥሶ ያለከልካይ መሆኑ ይመዘገብልኝና ወደ ሌላው ክርክር እንቀጥል። ይሄ ጨዋታ ይቁም። እኔ የፍርድ ቤቱን ጊዜ በዚህ ማባከን አልፈልግም። እናንተ የምትችሉትን ሁሉ አድርጋችኋል። ከዚህ በላይ አልጠብቅም” ሲሉም ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። 

በችሎት የተሰየሙት ሶስት ዳኞች ተከሳሽ፣ ጠበቆች እና የችሎት ታዳሚያን በሌሉበት ለደቂቃዎች ከተመካከሩ በኋላ፤ በፍቺ ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለመስጠት መነሻ የሆነው፤ አቶ ልደቱ ላለመፈታታቸው “ምክንያት ነው” የተባለውን እና በታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ “ተነግሮኛል” ያሉትን በመንተራስ ነው። 

“ትላንት 10 ሰዓት 25 ላይ አንድ ፖሊስ የታሰርኩበት ፖሊስ ጣቢያ መጥቶ፤ ‘መዝገብ ላይ ፈትተንህ እንደገና ያሰርንህ መሆኑን እንድታውቅ ነው’ ብሎ ነው የነገረኝ። እኔ ለአንድም ሰከንድ ከእስር ቤት አልተፈታሁም” ሲሉ መስከረም ላይ በመዝገብ ላይ እንደተፈቱ እንደተነገራቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “ክቡር ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቴን ያስጠበቀው፤ መቶ ሺህ ብር ያስያዝኩት፣ ፋይል ላይ ተፈትተሃል ለመባል ከሆነ ይሄ በፍትህ ቁማር መጫወት ነው” ሲሉም አክለዋል። 

ፍርድ ቤቱ “በደሴት ላይ” ለብቻው እንደማይኖር እንደሚገነዘቡ ለችሎት የገለጹት አቶ ልደቱ፤ ፍርድ ቤቱ የተቻለውን ቢያደርግም ህግ ተጥሶ እስካሁን ተይዘው መቆየታቸውን አብራርተዋል። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጣሱ እንደማያከራከር የጠቀሱት የመሃል ዳኛ፤ “ህግ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግስትም ነው የተጣሰው” ሲሉ ተናግረዋል። 

የመሃል ዳኛው ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረቡትን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይን በሚያነጋግሩበት ወቅትም ጠንከር ያሉ አባባሎች ሲጠቀሙ ተደምጠዋል። የፖሊስ ኮሚሽን ተወካዩ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉት አቶ ልደቱ እስካሁን ያልተፈቱበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ነበር። ኮሚሽኑ አቶ ልደቱን ያልለቀቀው ከቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ ያገኘው ምላሽ ላይ በመመርኮዝ መሆኑን ትላንት ለፍርድ ቤቱ ባስገባው ደብዳቤ ማስረዳቱን የመሃል ዳኛው አብራርተዋል። 

የቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ “አቶ ልደቱ ሕገ መንግስት በመናድ ተጠርጥረው ስለተከሰሱ፤ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት አትልቀቋቸው ተብለናል” የሚል ምላሽ እንደሰጠ በዛሬው የችሎት ውሎ ተነግሯል። የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ መሃል ዳኛ “እኛ ትዕዛዝ የሰጠነው መቶ ሺህ ብር ዋስትና ስለተፈቀደበት ነው። ምን አይነት ጉድ እንደሆነ እኮ ነው የማናውቀው። አንዱ ሲደበቅ፤ አንዱ ይወጣል። ገባ ወጣ ጨዋታ ሆኗል” ሲሉ በገረሜታ በታጀብ ድምጽ ሁኔታውን ገልጸውታል። 

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መከበር እንዳለበት ለቢሾፍቱ ፖሊስ በችሎት በተደጋጋሚ እንደተነገራቸው የመሃል ዳኛው አስታውሰዋል። በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተያዘው መዝገብ ላይ፤ ከፈለጉ በዚያው ማሳገድ እንጂ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም አሻፈረኝ ማለት እንደማይገባ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ በስተመጨረሻም የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አቶ ልደቱ አያሌውን በአንድ መዝገብ ፈትቶ፣ በሌላ ማሰሩን የሚያሳይ ማስረጃ ለነገ ሐሙስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here